ማየት የተሳናቸው እና የእይታ እክል ያለባቸው ሰዎች መምሪያ (DBVI) ማየት የተሳናቸው፣ መስማት እና ማየት የተሳናቸው ወይም የእይታ እክል ያለባቸው ሰዎች መድረስ የሚችሉበት ከፍተኛ የሥራ፣ የትምህርት እና ራስን የመቻል ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ለመርዳት ጥራት ያላቸው አገልግሎቶችን በማቅረብ ተግቶ ይሠራል። መምሪያው በሁሉም የዕድሜ ክልል ለሚገኙ ማየት የተሳናቸው የVirginia ነዋሪዎች ራስን ለመቻል ወሳኝ የሆኑትን ክህሎቶች፣ በራስ መተማመን እና አዎንታዊ አመለካከት እንዲያካብቱ ለመርዳት የተለያዩ ልዩ አገልግሎቶችን ያቀርባል።
ዋነኛ ትኩረታችን ማየት የተሳናቸው የVirginia ነዋሪዎች ከሥራ ቅጥር ጋር የተያያዘ ውጤት እንዲያገኙ በመርዳት ላይ ነው። ተጠቃሚዎችን በመንግሥት እና በግል ዘርፎች ውስጥ ሥራ ማግኘት እንዲችሉ ለመርዳት የሙያ ግምገማ፣ የሥራ ስልጠና፣ የሥራ እድገት፣ ምደባ፣ ክትትል እና ሌሎች አገልግሎቶች ይቀርባሉ። በምግብ አገልግሎት አስተዳዳሪነት እና ሻጭነት ዙሪያ የሚሰጡ ስልጠናዎች እና የሥራ ዕድሎችን በካፍቴሪያዎች፣ በቁርሳ ቁርስ ቤቶች እንዲሁም የመንግሥት እና የግል ህንፃዎች ውስጥ በሚገኙ ሌሎች የሽያጭ ተቋማት ማግኘት ይቻላል። የVirginia Industries for the Blind ማየት ለተሳናቸው የVirgia ነዋሪዎች በCharlottesville እና Richmond በሚገኙት ሁለት ፋብሪካዎቹ፣ በሳተላይት መደብር እንቅስቃሴዎቹ ውስጥ እና በመላው ኮመንዌልዝ በሚያከናውናቸው የአስተዳደር አገልግሎት ሥራዎቹ አማካኝነት ሌላ የሥራ ዕድል አማራጭ ያቀርባል።