የVirginia ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የቤት ውስጥ ግንኙነት ጉዳዮች ዙሪያ የሰርክዩት ፍርድ ቤቶች የሚሰጡት ውሳኔዎች ላይ፣ አስተዳደራዊ ኤጀንሲዎች የሰጧቸው ውሳኔዎች ላይ፣ የትራፊክ ደንብ ጥሰቶች ላይ እና የወንጀል ፍርድ ከተላለፈባቸው ክሶች በስተቀር የወንጀል ጉዳዮችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የሚቀርቡ የይግባኝ ጥያቄዎችን ይገመግማል። የVirginia የሠራተኛ ካሳ ኮሚሽን የሚሰጣቸው የመጨረሻ ውሳኔዎች ላይ የሚቀርቡ የይግባኝ ጥያቄዎችንም ይሰማል። የወንጀል እና የትራፊክ ጉዳዮች፣ የተሸሸጉ መሳሪያዎች ይዞ የመንቀሳቀስ ፈቃድ ለማግኘት የቀረቡ ማመልከቻዎች ላይ የተሰጡ የመጨረሻ ውሳኔዎች እና በከባድ ወንጀል ክርክሮች ላይ የሚሰጡ አንዳንድ ቅድመ ብይኖች ዙሪያ የሚቀርቡ የይግባኝ ጥያቄዎች መጀመሪያ በአቤቱታ መልክ መቅረብ የሚኖርባቸው ቢሆንም፣ ሌሎች የይግባኝ ጥያቄዎች በሙሉ እንደ መብት የተያዙ ናቸው። ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ ጥያቄዎችን የመስማት ስልጣን በሚኖረው ጉዳዮች ላይ በሙሉ የማንዳሙስ ትዕዛዞችን፣ እገዳዎችን እና ሃቢየስ ኮርፐስ ትዕዛዞችን እንዲሁም ከጥፋት ነፃነት መግለጫ (ባዮሎጂ-ነክ ያልሆነ ማስረጃ ላይ የተመሰረተ) ትዕዛዞችን የማስተላለፍ ስልጣን አለው።
የእስር ቅጣት ባልተጣለባቸው የትራፊክ ደንብ ጥሰት እና መጠነኛ የሕግ ጥሰት ጉዳዮች ላይ፣ የቤት ውስጥ ግንኙነት ጉዳዮች ላይ እና በአስተዳደራዊ ኤጀንሲዎች ወይም የVirginia የሠራተኛ ካሳ ኮሚሽን ፊት የሚነሱ ጉዳዮች ላይ የVirginia ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ይሆናል። ይሁን እንጂ የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ወሳኝ የሆነ ጉዳይ ዙሪያ ጉልህ ሕገ-መንግስታዊ ጥያቄ የሚያስነሳ ከሆነ ወይም ከፍተኛ ደረጃ ያለው እሴትን የሚወክል ጉዳይ መሆኑን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ መረዳት ከቻለ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም እነዚህን ውሳኔዎች ሊመረምር ይችላል። የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ ውሳኔዎች የመጨረሻ ከሚሆኑበት ሁኔታዎች ውጪ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ውሳኔ ቅሬታ የተሰማው ማንኛውም ወገን ይግባኝ ለመጠየቅ ለይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ አቤቱታ ማቅረብ ይችላል።